የአርባ ምንጭ ፓርክላንድ ኮሌጅ ከ1000 በላይ ተማሪዎችን ለሁለተኛ ጊዜ በተሳካ ሁኔታ አስመርቋል
31 August 2024
አርባምንጭ ፣ነሐሴ 25/2016 ዓ.ም ጋሞ ዞን(መ/ኮሚዩኒኬሽን)፦ ተመራቂ ተማሪዎች የሙያ ስነምግባርን አክብረው ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉም ጥሪ ቀርቧል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጋሞ ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ እሸቱ አልቶ ተመራቂ ተማሪዎች በኮሌጅ ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም በሰለጠኑበት ሙያ ብቁ እና አምራች ዜጋ በማፍራት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኮሌጁ ባለፉት 2 ዓመታት ከዞኑ መንግስ ጋር በመቀናጀት በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ በመሰማራት እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ እና በአቅም ውስንነት ምክንያት መማር ላልቻሉ 150 ተማሪዎች ለሰጠው የትምህርት እድል አመስግነዋል።
የአርባ ምንጭ ፖርክላንድ ኮሌጅ ባለቤት እና ዲን እጩ ዶ/ር ቴዎድሮስ ፋንታዬ ተመራቂዎች ወደ ስራ አለም ሲገቡ የሙያ ስነ ምግባርን አክብረው ከማገልገል ባሻገር ለሰለጠኑበት ዘርፍ መሻሻል የበኩላቸውን አስተዋፅኦም እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።
ተቋሙ ለ2ኛ ዙር በ 7 የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 1020 ተማሪዎች በድፕሎማ እና ከደረጃ 1 እስከ 4 በአካውንቲንግ ና ፋይናንስ፣ በሂማን ሪሶርስ፣ ማርኬቲንግ ፣ በማኔጅመንት ፣ በላይብረሪ የትምህርት መስኮች እና በተጨማሪም በአጫጭር ጊዜ ስልጠና በኢንግሊዝኛ ቋንቋ ፣ መሰረታዊ የኮሚፒውተር ክህሎትእና መሰል ስልጠናዎችን ከአንድ ወር እስከ አንድ አመት እንደሚሰጥም አስታውቀዋል።
በቴክኒክ እና ሙያ የትምህርት መስኮች ተማሪዎች ትምህርታቸውን በብቃት መፈፀማቸውን በብቃት ምዘና(COC) ፈተናን በመውሰድ ከደረጃ አንድ እስከ 4 ከተፈተኑ ተማሪዎች ከ95 በመቶ በላይ ማሳለፍ መቻሉን እጩ ዶ/ር ቴዎድሮስ ፋንታዬ ተናግረዋል ።
ኮሌጁ ከመማር ማስተማሩ አምድ በተጨማሪ በሀገር አቀፍ፣ በክልል እና በዞን ደረጃ በሚደረጉ ሰብአዊና እና ማህበራዊ ድጋፎች ላይ ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱንም አስታውሰዋል።
ፖርክ ላንድ ኮሌጅ በ2ኛ ዙር ካስመረቃቸው ተማሪዎች 7 በቀጥታ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ሲሆን 13 በውድድር ኮሌጁን እንደሚቀላቀሉ የኮሌጁ ዲኒ እጩ ዶ/ር ቴዎድሮስ ፋንታዬ አስታውቀዋል።
ኮሌጁ ለዚህ ደረጃ እንዲደርስ የዞኑ መንግስት እና ከተማ አስተዳሩ ላበረከቱት አስተዋጽኦም አመስግነዋል።








